ሐምሌ 12/2015
የአማራ ወጣቶች ማህበር ዋና ፀሀፊ ብሩክ ስለሽ ደብረብርሃን ላይ ሲታፈን ለስራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ የሄዱ የአማራ ተወላጅ ወጣቶች ደግሞ አዲስ አበባ ላይ በገፍ መታፈናቸውን የኢትዮ 360 ምንጮች አስታወቁ።
የአማራ ወጣቶች ማህበር ለኢትዮ 360 በላከው መግለጫው የአማራ ወጣቶች ሰብሳቢ የሆነው ብሩክ ስለሽ በኦህዴዱ አፋኝ ቡድን መታሰሩን ተናግረዋል።
ብሩክ ስለሽ ትላንት በዚሁ አፋኝ ቡድን እጅ ይግባ እንጂ አስቀድሞም ይሄው ህገወጥ ቡድንና ግብረ አበሮቹ ላለፉት ወራቶች ሲያሳድዱት መቆየታቸውን አንስቷል።
ሰብሳቢው ብሩክ ስለሺ ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ ያለበትን ለማግኘት ማህበሩ ባደረገው ማጣራት በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኘው የአኳሴፍ የውሃ ማምረቻ በነበረውና አሁን ላይ ይኼው አፋኝ ቡድን ለካምፕነት እየጠቀመበት የሚገኘው ስፍራ እንደሚገኝ ማረጋገጡን ገልጿል።
የአማራ ወጣቶች ማህበር በአሁኑ ሰዓት ይኼ ጨፍጫፊ ስርዓት በሰብሳቢው ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም አይነት ጉዳት ተጠያቂው ይኼ አፋኝ ቡድን እና ግብረ አበሮቹ እንደሆኑ ሊያውቁት ይገባል ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተመረቁ የአማራ ተወላጆች ለስራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ በሔዱበት በዚሁ ህገወጥ ቡድን በገፍ መታሰራቸውን የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
ያለምንም ጥፋታቸውን በየቦታው የስራ ማስታወቂያዎችን በማንበብና በየመስሪያ ቤቱ ስራ ለመጠየቅ የሚሔዱ የአማራ ተወላጅ ወጣቶች ሁሉ በዚሁ ቡድን መታፈናቸው ቀጥሏል ብለዋል።
እስካሁን ከየአካባቢው በገፍ እየታፈነ ያለውን ህዝብ ቁጥር ማወቅ አስቸጋሪ ነው የሚሉት የኢትዮ 360 ምንጮች በየማጎሪያው ያሉት ታሳሪዎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞም ውሃና የሚቀመስ ነገር ማግኘት ብርቅ እየሆነ መቷል መምጣቱን አስታውቀዋል።