በምስራቅ፣በሆሮጉድሩና በቄለም ወለጋ ዞኖች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን ላይ ዳግም እልቂት ለመፈጸም ወደ አካባቢው ገዳይ ቡድኑን የማጋዙ ስራ አሁንም መቀጠሉን ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 ገለጹ።
በከፍተኛ ሁኔታ እየገባ ያለው ገዳይ ቡድን ዋና ትኩረቱን የኪረሙ ወረዳዋ ሃሮ አዲስ አለም ላይ ቢሆንም እነ ጊዳ አያና፣ጉትና ሌሎች አካባቢዎች ከሐምሌ 5 ጀምሮ እያስወረረ ነው ብለዋል።
የዚህ ገዳይ ቡድን ወደ አካባቢው እንዲገባ የተደረገ ለሌላ ሳይሆን ራሱን ተከላክሎ በህይወት የተረፈውን የአማራ ተወላጅ መጨረስ ነው ብለዋል።
አማራ ክልል ላይ ትጥቅ አስፈታለሁ ብሎ ጦርነት የከፈተው አካል ወለጋ ላይ ደግሞ በደንብ ያሰለጠነውንና መሳሪያ ያስታጠቀውን ገዳይ ቡድን እያስወረረ ነው ሲሉ ለኢትዮ 360 ገልጸዋል።
በአካባቢው ያለው የአማራ ተወላጅ ህይወቱን ለማቆየት እንደምንም ብሎ እየታገለ ባለበት በዚህ ወቅት ደግሞ ገዳይ ቡድን ተልኮበታል ብለዋል።
የአሁኑ ስብስብ ደግሞ ከተለያየ ቡድን የተዋቀረና በደንብ ስልጠና እንዲወስድ የተደረገ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም።