በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ኢቲቪ የተጀመረው የሰራተኛውን የትምህርት ማስረጃ የመመርመር ስራ አመራሩን የሚያጋልጥ ሆኖ በመገኘቱ እንዲታፈን መደረጉን የኢትዮ 360 የውስጥ ምንጮች ገለጹ።
የሰራተኛውን የትምህርት ማስረጃ እንዲመረምር ተቋቁሞ የነበረ ኮሚቴ እንደነበር ይናገራሉ።
ነገር ግን ይሄ ኮሚቴ በራሱ ያጠናው ጥናት ምን እንደሆነና ምን ላይ እንደደረሰ ባይታወቅም ከትምህርትና ስልጠና ቢሮ የኢትዮ 360 የውስጥ ምንጮች ያገኙት መረጃ ግን ወደ 826 የሚሆኑ ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ የሃሰት መሆኑን አመልክተዋል።
ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዞ የተገኘው አመራሩና ያለምንም ውድድር ከሌለ መስሪያ ቤት መተው እንዲመደቡ የተደረጉት ባለጊዜዎች መሆናቸውን የውስጥ ምንጮቹ አጋልጠዋል።
ይሄን የተመለከተው የሰው ሃብት አስተዳደር ክፍሉም ከላይኛው አመራር ጋር በመነጋገር መረጃው ታፍኖ እንዲቀመጥ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
በተቋሙ ያለው ብልሹ አሰራር ከቀን ወደ ቀን እየተወሳሰበና ህገወጥነቱ እየበዛ ነው የሚሉት የውስጥ ምንጮቹ አዲስ ህንጻ ገነባሁ በሚል የተሰራው ከፍተኛ የሆነ ሸፍጥን ኢትዮ 360 በተደጋጋሚ ማጋለጡንም አንስተዋል።
አሁንም ይሄ ሳያንስ አሮጌ እቃዎችን ገጣጥሞ በአስቸኳይ ህንጻውን ለቃችሁ ውጡ በሚል አመራሩን ቢሮ ድረስ በመሄድ ሲያስፈራራ የነበረው የሰው በላው ስርአት መሪ አሁን ደግሞ ከአፍሪካ ቀደምት የሆነ ሚዲያ ገነባን የሚል አጀንዳን እንዲያራምዱ ጥብቅ መመሪያን ማውረዱንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
በየጊዜው የገነነ ስሙ እንዲጠፋና በህዝብ ዘንድ የነበረው ተቀባይነት እንዲጠፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የአሁኑ ኢቢሲ ከመሃል ከተማ ተነስቶ እንዲባረር የተደረገውም ቦታው ለአረብ ባለሃብቶች ለመሸጥ ከተደረገው ውል ጋር ተያይዞ መሆኑንም ኢትዮ 360 በመረጃው ማጋለጡ ይታወሳል።
Comments