ከአማራ ክልል ለህዳሴው ግድብ ደን ምንጠራ በሚል ወደ አካባቢው ከተወሰዱትና ከባድ ድብደባ እየተፈጸመባቸው ካለው ወጣቶች 8ቱ ህይወታቸው ማለፉን የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
ኢትዮ 360 በቅርቡ በ7 የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ለምንጠራ ስራ በሚል በርካታ ወጣቶች ወደ ስፍራው መወሰዳቸውን በመረጃው ማውጣቱ ይታወሳል።
እነዚህ ወጣቶች ወደ ቦታው ከሄዱም በኋላ የተሰጣቸውን ስራ ጨርሰው በኋላ ደሞዛቸው ተከፍሏቸው ወደ መጡበት እንዲመለሱ ቢጠይቁም ምላሹ ግን እስርና ድብድባ እንዲሆን መደረጉንም ኢትዮ 360 ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
በተለይ ወጣቶቹ ምግብና ውሃ እንዳያገኙ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በየቀኑ የሚደርስባቸው ድብደባ ህይወታቸውንና አካላቸውን እንዲያጡ አድርጓቸዋል ብለዋል።
በእባብና በጊንጥ እየተነደፉ የሚሞቱ ወጣቶች ቁጥርም ከፍተኛ መሆኑን ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ደሞዛቸው ቀርቶባቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመልሷቸው ቢጠይቁም ያንን ከማድረግ ይልቅ ድብደባንና ማሰቃየትን ስራዬ ያለው አካል ወጣቶቹን እየገደላቸው ነው ሲሉ የኢትዮ 360 ምንጮች የሚፈጸመውን ኢሰብአዊ ድርጊት አጋልጠዋል።