በአፋር ክልል የሰው በላው ስርአትን የሚቃወሙ ጽሁፎችን ደግፋችኋል በሚል ወደ 20 የሚጠጉ አመራሮችና ወጣቶች መታሰራቸውን የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
የክልሉ የለውጥና መልካም አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ሃንፍሬ መሃመድን ጭምሮ በርካቶች ለእስር የተዳረጉት ምንም አድርገው ሳይሆን በማህበራዊ ድረገጽ የሚሰራጩና ገዳዩን ስርአት የሚያወግዙ ጽሁፎችን ደግፋችኋል በሚል መሆኑን ያነሳሉ።
ልክ እንደ አቶ ሐንፍሬ ሁሉ በቅርብ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ሲሰሩ የነበሩና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚሰሩ ስህተቶችን ሊያርሙ ይሞክሩ የነበሩ አመራሮች ሁሉ ወደ ማፈኛ ስፍራ መጋዛቸውን ተናግረዋል።
በጅምላ የሚደረገውን ይሄንን አፈና ትእዛዝ ከመስጠት ጀምሮ እስክ ተፈጻሚነቱ ድረስ ያለው ስራ የሚሰራው ደግሞ በፕሬዝዳንቱ አወል አርባና በፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሰልፈዲን አማካኝነት መሆኑን ነው ምንጮቹ የሚናገሩት።
አመራሮቹንም ሆነ ወጣቶችን ሰብስቦ ሰመራ ወደሚገኝ ማፈኛ ስፍራ የወሰደው አካል እስካሁን ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ አለማድረጉንም ገልጸዋል።
ከዛም አልፎ ታሳሪዎቹ ታፍነው አንድ ቦታ ታሽገው እንዲቀመጡ ከመደረጉም በላይ ከቤተሰቦቻቸውም ጋር ሆነ ከማንኛውም ሰው ጋር እንዳይገናኙ መደረጋቸውንም ነው የኢትዮ 360 ምንጮች የገለጹት።
እነ አቶ ሐንፍሬ ወደ ማፈኛ ስፍራ መውሰዱ ያልበቃው አካል አሁንም አይን ውሃቸው አላማረኝም ያላቸውን ሁሉ እየሰበሰበ ማሰሩን ቀጥሏል ሲሉ የኢትዮ 360 ምንጮች ገልጸዋል።
Comentários