በአዲስ አበባ ቤተመንግስት ዙሪያ በጥበቃ ስራ ተሰማርተው የነበሩ ከ250 በላይ የአማራ ተወላጆች ትጥቅ እንዲፈቱ ተደርገው በብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ መታሰራቸውን የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
እነዚህ የአማራ ተወላጅ የሆኑ የሰራዊቱ አባላት ለረጅም አመታት በታማኝነት ቤተመንግስቱንና አካባቢውን ሲጠብቁ የኖሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ነገር ግን ሰው በላው ስርአት መምጣቱን ተከትሎ ግን ውስጥ ለውስጥ ከፍተኛ የሆነ መገለል ሲፈጸምባቸው መቆየቱን ይናገራሉ።
ይሄንን ሁሉ መገለልና የተለያዩ ጫናዎች ሲያደርስባቸው የቆየው አካል አሁን ደግሞ መሳሪያቸውን ነጥቆ ወደ ብላቴ ማሰልጠኛ ማእከል እንዲወሰዱ አድርጎ አፍኗቸዋል ብለዋል::
እንደ ምንጮቹ ከሆኑ ከ250 በላይ የሚሆኑት የአማራ ተወላጆች ወደ ብላቴ ተወስደው መታሰራቸውን እንጂ ወደዛ ከተወሰዱ በኋላ ግን ስለተፈጸመባቸው ሰብአዊ ጥሰት የታወቀ ነገር የለም ይላሉ።
አሰበ ተፈሪ ላይ መሳሪያቸውን አስቀምጠው ስፖርት ሲሰሩ ከነበሩት የመከላከያ አባላት መካከል በብሄራቸው ተመርጠው የተገደሉት የአማራ ተወላጆችን ጨምሮ በየአካባቢው የሚገደሉ የአማራ ተወላጅ የሰራዊቱ አባላት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
በቅርቡ ወለጋ ላይ በዛው ተወልደው ያደጉና የሰራዊቱ አባላት የነበሩ የአማራ ተወላጆችም በአደባባይ ተመርጠው መገደላቸውን ኢትዮ 360 በመረጃው ማውጣቱ ይታወሳል።