የብርሃኑ ጁላና የይልማ መርዳሳ ጦር በአየርና በምድር በቆቦና በዞብል ተራራ አካባቢ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጦርነት መክፈታቸውን የኢትዮ 360 ምንጮች አስታወቁ።
የይልማ መርዳሳ አየር ሃይልም ይሁን የብርሃኑ ጁላ የምድር ጦር በጋራ ጦርነቱን የከፈቱን በፋኖ ህዝባዉ ሃይል ላይ ነው ይባል
እንጂ ጥቃቱ ግን በዋናነት ያነጣጠረው በንጹሃን የአማራ ተወላጆች ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
በአካባቢው ያለው የምስራቅ አማራ ፋኖም ባለ በሌለ ሃይሉ በግፍ እየተገደለ ያለውን ወገኑን ለመታደግ ከዚህ ገዳይ ቡድን ጋር አንገት ለአንገት መተናነቁን ይናገራሉ።
በተዋጊ ጀቶች ጭምር እየተካሄደ ያለው ጦርነትን ለማገዝ ወደ አካባቢው ሲጓዝ የነበረ ዙ23 መሳሪያ ሮቢት ላይ በምስራቅ ፋኖ ህዝባዊ ሃይልና በህብረተሰቡ ትብብር እንዲወድም መደረጉንም ያነሳሉ።
በካራይላ አከባቢ በሚገኙ ተራራማ ስፍራዎችን ጨምሮ በቆቦና አካባቢው ንጹሃንን ለመጨረስ የመጣው የኦህዴዱ የመከላከያ አንገት ለአንገት የተናነቀውን የምስራቅ አማራ ፋኖን መቋቋም ባለመቻሉ በአገኘው ሁሉ እግሬ አውጪኝ ማለቱን ምንጮቹ ይናገራሉ።
ከምስራቅ አማራ ፋኖ ባልተናነሰ ሁኔታም ህብረተሰቡ ከዚሁ ገዳይ ቡድን ጋር ፊት ለፊት መጋጠሙንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
በራያ ቆቦ ዛሬ ለሊት ከ11 ሰአት 30 ሰዓት የጀመረው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው የሚሉት የኢትዮ 360 ምንጮች የአካባቢው ማህበረሰብም ቀዬውን ለቆ ከመሸሽ ይልቅ ከልጆቹ ጎን ሆኖ ገዳይ ቡድኑን ፊት ለፊት ተጋፍጦታል ብለዋል።
ይሄ ሁሉ የቦምብ ውርጅብኝም ሆነ የከባድ መሳሪያ ጥቃት በህዝቡ ላይ የተከፈተው ለሌላ ሳይሆን ራያና አካባቢውን እሰጥሃለሁ ተብሎ ቃል የተገባለትን የህወሃቱ ቡድንን ለማስደሰት ነው ሲሉም ምንጮቹ ገልጸዋል።
ቆቦ ከተማን ጨምሮ አራዱም፣ አሳመምቻ፣ ቀመሌ ተክለሀይማኖት፣ ጠዘጠዛ፣ ካራይላ፣ አራዱም እና ሮቢት ዙሪያ ያሉ አከባቢዎች በሙሉ በጦርነት እየታመሱና ህዝቡ ከዚሁ ገዳይ ቡድን ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ቀጥሏል ይላሉ።
ከንጋት 11:30 ጀምሮ በሰው በላው ስርአት በተከፈተው ጥቃት የአላማጣ ከተማ ሆስፒታል፣ የቆቦ ከተማ ሆስፒታል እና የወልድያ ከተማ ሆስፒታልን ጨምሮ በየአካባቢው ያሉ ጤና ጣቢያዎች በዚሁ ቡድን ቁስለኛ መሞላታቸውን አንስተዋል።