top of page

ሐምሌ 6/2015የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ በሚገኙ የኤጲስ ቆጶስነት ምርጫ እንዲቆም ሲል ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ አሳለፈ፡፡


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ በሚገኙ አህጉረ ስብከት የተመደቡ አባቶች እናደርገዋለን ያሉት የኤጲስ ቆጶስነት ምርጫ ሕገ ቤተክርስቲያንን ያልተከተለ በመሆኑ እንዲቆም ሲል ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ አሳለፈ፡፡


ቅዱስ ሲኖዶሱ ሐምሌ 5 እና 6 ቀን 2015 አመተ ምህረት ለሁለት ተከታታይ ቀናት ያካሄደውን ስብሰባ በማጠናቀቁን ተከትሎ መግለጫውን አውጥቷል።


ሲኖዶሱ በትግራይ በሚገኙ አህጉረ ስብከት የተመደቡ አባቶች የቅዱስ ሲኖዶስ የሰላም ጥሪን ቸል ከማለትም አልፈው ሐምሌ 9 ቀን 2015 እናደርገዋለን ያሉት የኤጲስ ቆጶስነት ምርጫ ሕገ ቤተክርስቲያንን ያልተከተለ ነው ሲል ገልጾታል።


ሂደቱን በማስቆሙ ረገድም የሚመለከታቸው አካላት ከቤተክርስቲያኗ ጎን እንዲቆሙ ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው ጥሪውን አቅርቧል።


ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ በክልል ትግራይ በተካሄደው ጦርነት በቤተ ክርስቲያናችን የበላይ መዋቅርና በክልል ትግራይ አህጉረ ስብከት መካከል የነበረው አስተዳደራዊ መዋቅር ተቋርጦ መቆየቱንም አንስቷል።


የተፈጠረው አለመግባባትም በውይይት ተፈቶ መዋቅራዊ አንድነት በድጋሚ ተጠናክሮ እንዲቀጠል ሃገራዊ የሰላም እርቁ ከተፈጸመበት ማግስት ጀምሮ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ፊርማ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ሲጠየቅ መቆየቱንም አስታውሷል።


ምንም እንኳን ቅዱስ ሲኖዶሱ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም በክልሉ ያሉት ብፁዓን አባቶችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተከፈተው የሰላምና የውይይት በር ከመጠቀም ይልቅ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በመጣስ መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት መሥርተናል በሚል ተገቢነት የሌለው መግለጫ መስጠታቸውን ገልጿል።


ከዛም አልፎ ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት መፈጸም አለበት የሚል ውሳኔ በማሳለፍ 10 ኤጲስ ቆጶሳትን ሐምሌ 9 ቀን 2015 ለመሾም ፕሮግራም መያዙን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ መስጠታቸውንም ተናግሯል።


በመሆኑም የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 19 ንዑስ ቁጥር 13 የሕግ ድንጋጌ መሠረት ሐምሌ 6 ቀን 2015 ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ገልጿል።


በትግራይ ክልል ሐምሌ 9 ይደረጋል የተባለው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የሕገ ቤተ ክርስቲያንና አንቀጽ 37 እና 38 ያላከበረና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር ተገቢ ያልሆነ የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊነት የሚጥስ ነው ሲል ገልጾታል።


ይሄ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚጎዳና በጦርነት የተጎዳውን ሀብት ንብረቱ የወደመበትን ገዳማቱና አብያተ ክርስቲያናቱ የተጎዱበትን ሕዝብ የማይጠቅም ተገቢነት የሌለው በመሆኑ እንዲቆም ሲል ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔውን አሳልፏል፡፡


በትግራይ ክልል ተከስቶ የነበረውን ችግር የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ችግሩን በውይይት የፈቱት መሆኑ እየታወቀ የሰላም ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን እስካሁን ሰላም መፈለጓ ያልተቋረጠ ቢሆንም አለመሳካቱ የሚያሳዝን በመሆኑ ለሰላም የሚደረገው ጥረት ዘላቂ መፍትሔ እስከሚገኝ ድረስ የማይቋረጥ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶሱ በውሳኔው አስፍሯል።


በመላው ዓለም የሚገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ሕዝበ ክርስቲያን እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ያስተላለፈችውን የሰላም ጥሪ ተግባራዊ ሆኖ አንድነቷ ጸንቶ ይኖር ዘንድ በጸሎት ተግተው ከቤተ ክርስቲያናቸው ጎን እንድትቆሙ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪውን አስተላለፏል፡፡


Recent Posts

See All

መስከረም 17/2016 በኢትዮጵያ አየር መንገድ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ሰራተኞች እየታደኑና እየታፈኑ መሆኑን ሰራተኞቹ ገለጹ።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ሰራተኞች እየታደኑና እየታፈኑ መሆኑን ሰራተኞቹ ገለጹ። ሰራተኞቹ እየታፈኑ ያሉት ደግሞ በውስጥ በተሰገሰጉ የሰው በላው ስርአት ሃይሎች ጥቆማ ሰጭነት መሆኑን ለኢትዮ 360...

መስከረም 17/2016 በሰሜን ሸዋ ሚዳ መርሃቤቴ ላይ ገድይ ያደረገ ህዝባዊ ሃይሉ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎችን ከሰው በላይ ሃይል ነጻማውጣታቸውን ገለጹ

መርጦ ለማርያምን ነጻ ያወጣው ህዝባዊ ሃይል መቅደላ አምባ አምባ ዩኒቨርስቲ ውስጥና በአካባቢው በሚገኝ ካምፕ ውስጥ መሽጎ የነበረውን ይሄንን ሃይል ማጽዳት ተችሏል ብለዋል። አሁን ላይ ከሁሉም አካባቢ የተባረረው ገዳይ...

መስከረም 17/2016 አርሶ አደሮችን በግፍ የረሸነውን ገዳይ ቡድን በአካባቢው ያለው የመብረቅ ጓሌ ሻለቃ ተከታትሎ በወሰደው ርምጃ ሁሉንም ማጽዳቱን ገለጹ

መስከረም 17/2016 አርሶ አደሮችን በግፍ የረሸነውን ገዳይ ቡድን በአካባቢው ያለው የመብረቅ ብርጌድ ጓሌ ሻለቃ ተከታትሎ በወሰደው ርምጃ ሁሉንም ማጽዳቱን ገለጹ። በጎንደር ዙሪያ ማክሰኝት ወረዳ የጭንጫዬ አርሶ...

Коментарі


bottom of page