በጉጂ ዞን በሊበን ወረዳ ለተጎጂው ማህብረሰብ የሚመጣው እርዳታ በአመራሩ እየተዘረፈ መሆኑ ህዝቡን በረሃብ እንዲያልቅ እያደረገው ነው ሲሉ ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 ገለጹ።
በአካባቢው መንግስት የለም ብቻ ሳይሆን ሕዝብን ያስገረሙና ሌብነትን ሕጋዊ ያደረጉ የብልጽግናው አመራሮች ህዝቡን አላስኖር ብለውታል ይላሉ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ።
ከአመራሩ በላይ በአደጋ መከላከል ውስጥ የሚሰሩት በሙሉ የተጎጂው ማህበረሰብ የሚመጣዉን እህል ከነመኪናዉ ለዱቄት ፋብሪካዎች ይሸጡታል ሲሉ ወንጀሉን ያጋልጣሉ።
በኦነግ ገዳይ ቡድን ከቀዬው የተፈናቀለው ህዝብ ደግሞ የሚቀምሰው አቶ በረሃብ እያለው ነው ብለዋል።
ከተማዉ በሙሉ እርዳታ በጫኑ ተሽከርካሪዎች የተሞላ ቢሆንም የሌቦቹ ስብስብ ግን እህሉን ብቻ ሳይሆን ተጭኖ የመጣውን ልባሽ ጨርቅ ሳይቀር አየር በአየር ለሽያጭ እንደሚያቀርቡት ይናገራሉ።
በቅርብ ይላሉ ነዋሪዎቹ ሙሉ መኪና እሕል የጫነ ተሽከርካሪ ከግቢው ሲወጣ ጣ ተረጂው ማህበረሰብ እያለቀሰ መንገዱን ዘግቶ እህሉን እንዲሰጡት ቢለምንም አሽከርካሪውን ግን እኔ እንጀራዬ ነዉ እዚህ ከምትጮሁ ሒዱና ለፖሊስ ጠቁሙ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውም ይናገራሉ።
በተባሉት መሰረትም ትንሽ አቅም ያላቸው ወንዶች ተሰባስበው ሔደው ለመጠቆም ቢሞክርቱም ጆሮ ሰቶ የሚያዳምጣቸው ሊያገኙ አልቻሉም ብለዋል።
የሌባው ስብስብ ዘርፎ በሚሸጠው የእርዳታ እህልና ልባሽ ጨርቅ ቤት በመገንባትና ባለሶስት እግር ባጃጅ በመግዛት ስራ ተጠምዷል ይላሉ።
አሁንም ተጎጂው ማህበረሰብ የድረሱልን ጥሪ ከማሰማት ሌላ ምንም ማድረግ አልቻለም የሚሉት ነዋሪዎቹ አሁን ከረሃቡ መጽናት የተነሳ ህይወታቸውን ማጣት ጀምረዋል ሲሉ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ አስፍረዋል።
Yorumlar