በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ድንበር ላይ የሚገኘውና አውራ ጎዳና የሚባለው አካባቢ በኦህዴዱ ሃይል መወረሩን ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 ገለጹ።
ከተማዋን የወረረው ይሄው ቡድን ቁጥራቸው በትክክል የማይታወቅ የአማራ ተወላጆችን በግፍ መጨፍጨፉን ይናገራሉ።
በአካባቢው የተፈጸመው ግፍ ሰቅጣጭ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ ይሄንን ድርጊት ፈጻሚው ደግሞ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ነው ይላሉ።
ወደ ከተማዋ የገዳዩ ቡድን የመከላከያ ሃይል ሲገባ ተከትሎት የገባው ልዩ ሃይሉ የአማራ ክልል አርማ እየተነቀለ የኦሮሚያ ክልል አርማ እንዲሰቀል አድርጓል ብለዋል።
በተጨማሪም ከኦሮሚያ ክልል በቀጥታ ብዛት ያላቸው ተሳቢ ተሽከርካሪዎችን ወደ ከተማዋ በማስገባት የከተማው ነዋሪዎችን ንብረት በሙሉ እየጫኑ ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲጋዙ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
ሞተር፣ ተሽከርካሪዎች ፤ባጃጆች፤ የቤት እቃዎች እንደ ቴሌቭዥን የአርሶአደሩ ጤፍ ፣እህል ሁሉ እየተጋዘ ወደ ኦሮሚያ ተወስዷል ባይ ናቸው።
የሚገርመው ደግሞ ይላሉ ነዋሪዎቹ ለዝርፊያ ከገቡት ተሽከርካሪዎች የተረፈውን ደግሞ ተከትሏቸው የመጣው ህግወጥ ስብስብ ወደ ከተማዋ ገብቶ በሙሉ አፅድቶታል ሲሉ የተፈጸመው አይን ያወጣ ሌብነት ይናገራሉ።
በአሁን ሰዓት ከተማዋ በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ቁጥጥር ስር ውላለች የሚሉት ነዋሪዎቹ ንብረቱ ተዘርፎ ባዶ እጁን እንዲቀር የተደረገው ማህብረሰብ በስልክ በመደወል ጭምር ከ100ሺህ ብር በላይ አምጡ በሚል መግቢያና መውጪያ እንዲያጣ ተደርጓል ብለዋል።
የለኝም ያለ ደግሞ በአደባባይ ይደበደባል ይሰቀላል ሲሉም እየተሰራ ያለውን ግፍ አጋልጠዋል።
ይሄንን ስቃይ መቋቋም ያልቻለው ህዝብ ቀየውን ለቆ ለመሰደድ ተገዷል ብለዋል ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ።