የኤርትራ መንግስት በተለያዩ አቅጣጫዎች ጦሩን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እያስጠጋ መሆኑን የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
ሻብእያ ከተሰነይ እና ከባሬንቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሃይል ወደ ተኮንብያ ማምጣቱም ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።
ይሄ ቦታ ደግሞ ከባድመ በቅርብ ርቀት የሚገኝ አካባቢ መሆኑንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
የሱዳኑ ግርግር ሲነሳ በዛ ያለውን ሃይል አንስቶ ወደ ተሰነይ ወስዶ ስምሪት ሲያደርግ የቆየው የሻአብያ ጦር አሁን ደግሞ ከዚህ ሃይሉ ላይ የተወሰነውን ወደ ተኮንብያ ማምጣቱን ገልጸዋል።
ከባሬንቱም የመጣው ሌላው ሃይል እንዲከማች የተደረገው በዚሁ ተኮንብያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑን ይናገራሉ።
በአብይ አህመድ ፈቃጅነት ለሰሜኑ ጦርነት ወደ ኢትዮጵያ የገባው ሃይል ባድመን እንዲቆጣጠር ተደርጎ በዛው መቅረቱን ሳይጠቁሙ አላለፉም።
አሁንም የሻእብያ ጦር ተኮንቢያ ላይ ሃይሉ በከፍተኛ ሁኔታ እያከማቸ ያለው ለሽራሮና ለሌው አካባቢ ቅርብ በመሆኑ ነው ይላሉ።
ሻእብያ ሃይሉን በዚህ ደረጃ እያስጠጋ ያለው ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ካለው አካል ጋር በመከዳዳታቸው መሆኑን አስቀምጠዋል።
ከሰንአፈ ወደ ኢትዮጵያ መሬት አይጋ ግንባር ሃይሉን እያስጠጋ ያለው ይሄው ቡድን ምናልባትም በቅርቡ ጦርነት ሊጀምር ይችላል ሲሉም ምንጮቹ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያን አስተዳድራለሁ የሚለው አካል አበበኩሉ አየር ሃይሉ ከፍተኛ ዝግጅት እንዲያደርግና በሶማሌ ጎዴ በኩልም ወታደራዊ ስልጠና ማስጀመሩን ይናገራሉ።
ምናልባትም የሁለቱ ቡድኖች በዚህ ሰአት ለጦርነት መዘጋጀት ከጀርባው የያዘው ሌላ አጀንዳ ሊኖር ይቻላል ሲሉም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
በአካባቢው ከባድ ጦርነት ለመጀመርና የህዝቡን ቀልብ ወደዛው ለመሳብ የጦርነት ጉሰማ እያሰሙ ያሉት ሁለት ቡድኖችን ከወዲሁ ተው ሊላቸው የሞከረ አንዳችም አካል አለመኖሩንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
Comments