የ40/60 በባለ አንድ መኝታ ቤት የጋራ መኖሪያ ቤት ኮንዶሚኒየም አጠቃላይ ክፍያን አጠናቆ ሰርቶ ለመስጠት የሚከፈለው 470,000 ሺ ብር ነበር ይላሉ ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ።
ነገር ግን ይሄን ብር አጠቃሎ ለከፈለው ደንበኛ ግን የተደረገው ነገር ብሎኬት ብቻ ገንብቶና ለስኖ ከዚህ በላይ መስራት አልቻሉም ራሳችሁ ጨርሱት በሚል ቁልፍ የሚያስረክብ አስተዳደር ነው ይላሉ።
በተለይ ቱሪስት ሳይት ተብሎ በሚጠራው የጋራ መኖሪያ ቤት ባለእድሎች የቤቱን ግንባታ ለማስጨረስ ከ650,000 ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።
ነገር ግን ይሄን ሁሉ አድርጎ ቤቱ ውስጥ ለመኖር የሞከረው ዜጋ 18 ፎቅን እቃ ተሸክሞ በእግሩ እንዲወጣ ተፈርዶበታል ብለዋል።
መኖር አልቻልንም የሚሉት ኢትዮጵያውያን ለቤታቸው የምትሆን ትንሽ እቃ ገዝተው ለማስገባት ህንጻው ፊት ለፊት የሚኮለኮለው ህገወጥ ቡድን 30ሺ ብር ካልከፈላችሁኝ በሚል የንብረት ንጥቂያ ላይ ተሰማርቷል ሲሉ በመረጃቸው ላይ አመልክተዋል።
በህንጻው ውስጥ ደግሞ 18 ፎቅ አይደለም አንድ ፎቅ መውጣት የማይችሉ ህሙማን መኖራቸውንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ለማን አቤት እንደሚባል ግራ ገብቶናል የሚሉት ነዋሪዎቹ አሁን ደግሞ ገና መኖር እንኳን ሳይጀምሩ ግብር ክፈሉ የሚል መመሪያ መምጣቱን በምሬት ተናግረዋል።
የሚገርመው ይላሉ ህንጻው ሳያልቅ ከ3 አመት በፊት ነው ከባንክ ጋር አዋውሎ የቤት እዳ ወለድ እንዲከፍሉ ሲደረጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።
መገናኛ 24 ሰፈር ጉሙሩክ ተብሎ በሚጠራውና ቱሪስት ሳይት በሚል የሚታወቀው የጋራ መኖሪያ ቤት ባለንብረቶች እየደረሰባቸው ያለውን በደል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሚመለከተው አካል አቤት ለማለት ቢሞክሩም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉም ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ገልጸዋል።
Comments