የሀገራ አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ጉዳይ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላትን ጉዳዩ ከግምት በማስገባት ፍርድ ቤቱ የአገልጋዮቹ የዋስትና መብት ተጠብቆ ከእስር እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥያቄ አቀረበ።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ይሄንን አስመልክቶም ለፍርድ ቤቱ ደብዳቤ መጻፉም ታውቋል።
በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፍቃድ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም የተዋቀረው የሀገራ አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ጉዳይ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ አክሊል ዳምጠው እና ጸሐፊው መምህር ተሾመ በየነ በእስር ላይ እንደሚገኙም ቅዱስ ሲኖዶሱ በደብዳቤው አስታውሷል።
የእነዚህን ሁለት አገልጋዮች የፍርድ ሁኔታ በተመለከተም ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ በጻፈው ደብዳቤ ኮሚቴው ቤተክርስቲያን የጣለችበትን ኃላፊነት ለመወጣት ሌት ከቀን ተግቶ እየሠራ መሆኑን በዝርዝር አስቀምጧል።
ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም በኮሚቴው የተሰጠው መግለጫም ቢሆን የዚህ ሥራ አካል መሆኑን አስምሮበታል።
በተጨማሪም በመግለጫው ላይ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመ ወንጀል አለ ብላ እንደማታምን በመግለጽ ወንጀል እንኳን ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሚዳኝ ይሆናል ሲልም በደብዳቤው ላይ አስቀምጧል።
እናም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ ከግምት በማስገባት የአገልጋዮቹ የዋስትና መብት ተጠብቆ ከእስር እንዲፈቱ ሲል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥያቄውን አቅርቧል።
Comments