የብልጽግናው ካድሬዎች በየቀበሌውና በየክፍለከተማው እየዞሩ የፓርቲውን መጽሔት እንዲሸጡ የወረደው መመሪያ ውስጥ ለውስጥ ቁጣን መቀስቀሱን የኢትዮ 360 ምንጮች አስታወቁ።
መጽሔቱን የመሸጡ ዘመቻ ከቀበሌና ከክፍለከተማ አልፎ በየሰፈሩ ሁሉ እንዲዞሩ ያዛል ይላሉ።
በብር እጦት እየተሰቃየ ያለው አካል መጽሔቱ በ20ብር እንዲሸጥ ሲወስን ሃሳቡም ልክ እንደ አባቱ ኢህአዴግ የፓርቲውን ፖሊሲዎች ብሎም ቀጣይ አጀንዳዎች ያጋጠሙት ተግዳሮቶች የሚፈትሽበትን"አዲስ ራዕይ" መጽሔትን ለማስመሰል መሞከሩን ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ነገር ግን ይሄንን መጽሔት ገና ከጅምሩ ለየት የሚያደርገዉ አስቂኝ ነገር ቢኖር ህዝባዊ ቅቡልነት አለኝ በሚል ህልም የሚጀምር መሆኑን ነው ይላሉ።
እንደመጽሔቱ ንጽጽርም አባትዬው ኢሕአዴግ የወደቀው በህዝባዊ ቅቡልነት እጦት ነው በሚል በራሱ ላይ የሚሳለቅ መሆኑ ነው ሲሉ ምንጮቹ ገልጸዋል።
አሁን መንግስት ነኝ ብሎ ራሱን የሚጠራው አካል ሃገሪቱን እየገዛ ያለው ህዝቡ ስለወደደው መሆኑን በመጽሔቱ ላይ በአዋጅ መልክ አስቀምጦታል ብለዋል።
እናም ይሄንን በስላቅ የተሞላ መጽሔት ሽጥ የተባለው ስብስብ ገና ከጅምሩ ከራሱ ካድሬዎች አንገዛም የሚል ምላሽ መሰማቱ ደግሞ ቁጣውን ውስጥ ለውስጥ እንዲካረር አድርጎታል ሲሉ ምንጮቹ ተናግረዋል።
ገና ከካድሬው ትችት የገጠመውንና ገበያ የራቀውን መጽሔት ይዞ ወደ ህዝብ ለመቅረብ ፈቃደኛ አለመሆኑ የእርስ በርስ ግብግቡን አካሮታል ሲሉ የኢትዮ 360 ምንጮች ገልጸዋል።
Comments