በኮንሶ ዞን ጉማይዴ አካባቢ የሚቀሳቀሰው ኮንሲታ የተባለው ህገወጥ ቡድን በሰገን ከተማ በአራቱም አቅጣጫ በዘመቻ መልክ ዝርፊያ መጀመሩን ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 ገለጹ።
ለዚህ እንዲያግዛቸው ደግሞ የህገወጥ ቡድኑን ስብስቦች የትራፊክ ፖሊስ ልብስ በማልበስ ጭምር ማሰማራቱን ይናገራሉ።
በአራቱም አቅጣጫ የሰገን ከተማ መግቢያና መውጫ በመክበብ አሽከርካሪዎችን በማስቆም ጭምር ዝርፊያውን አጧጡፎታል ብለዋል ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ።
ይሄን ተከትሎም በሕዝቡ ውስጥ ቁጣ የተቀሰቀሰ ሲሆን የአካባቢው ሽማግሌዎች የሌባውን ስብስብ ከማስቆም ይልቅ ህዝቡን እናረጋጋለን ብለው በመነሳታቸው በርካታ ወጣቶች በዚህ የታጠቀ ሃይል እንዲደበደቡና እንዲታፈኑ ሆነዋል ብለዋል።
ወጣቶቹ እየተደበደቡ መታሰር ባቻ ሳይሆን በዚሁ ቡድን ሞተር ብስኪሌቶቻቸው ሁሉ ተዘርፈዋል ሲሉም በመረጃቸው አመልክተዋል።
አሁን ካለው ከባድ ሁኔታ አንጻር በቀጣዮቹ ቀናቶች ምን ልፈጠር እንደሚችል ለመገመት ከባድ ነው ብለዋል።
በእርቅ ሰበብ የሕዝቡን ጥያቄ ለማዳፈን እየጣረ ያለው የካድሬ ስብስብ ደግሞ በአካባቢው ጠንካራና ህዝብ አንቂ ናቸው የሚባሉ ግለሰቦች በመጠቆም ቤት ለቤት እያስለቀመ መሆኑንም ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።