ከአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች እየታፈኑ የሚታሰሩ የአማራ ተወላጆችም ሆኑ ሌሎቹ በየማፈኛ ቤቱ ካለው የእስረኛ አያያዝና ድብደባ ጋር ተያይዞ ለከባድ ህመም ሊጋለጡና ህይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ታፋኞቹ ለኢትዮ 360 ገለጹ።
በአዋሽ፣በጦር ሃይሎች፣በኢንደስትሪያል ፓርክ፣በቱሉ ዲምቱ፣በሲኤሚ ሲና በተለያዩ አካባቢዎች፣የግለሰቦችን ቤት ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች በከባድ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
ሰሞኑን ከተለያዩ ማጎሪያ ስራዎች የወጡ የአማራ ተወላጆች ለኢትዮ 360 ባደረሱት መረጃ ላይ ከእስሩና ከእንግልቱ በላይ ከማፈኛ ስፍራው ጠባቂዎች የሚወጣው ሰብአዊነት የጎደለው ስድብ የህሊና እስረኞችን ሰላም የሚነሳ ነው ይላሉ።
ስድቡ አልበቃ ያለው ደግሞ ምንም አይነት ምክንያት ሳያስፈልገው ታፋኞቹን እያስወጣ እስኪደክመው ሲደበድብ ይውላል ሲሉ የሚሰራውን የጭካኔ ተግባር ይመሰክራሉ።
ይሄንን ሁሉ ስድብና ዱላ የሚቀበለው ታሳሪ ይሄ ሁሉ የሚወርድበት ደግሞ በቀን አንድ ኮቾሮ ወይንም አልፎ አልፎ የምትወረወርለትን አንድ ዶቦ በቀመሰ አንጀቱ ነው ሲሉ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ አስፍረዋል።
በአንዳንዶቹ ማጎሪያ ስፍራዎችን ንጹሃን ዜጎቹ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ ለሶስትና ለአራት ቀን ምንም አይነት ምግብም ሆነ መጠጥ እንዳይሰጣቸው እንደሚደረግም አመልክተዋል።
አብዛኛው ታሳሪ እንዲታጎር የተደረገበት ቆርቆሮ በቆርቆሮ በተሰራ መጋዘን ውስጥ መሆኑ በራሱ ሙቀትና ብርዱ እንዲፈራረቁበት አድርጎታል ብለዋል።
አንድም ወንጀል ሳይሰራ ተመርጦ ባልተወለደበት ብሔሩ በገፍ እየታሰረ ያለው የአማራ ተወላጅም ሆነ ሌላው በየማጎሪያ ስፍራው እርስ በርስ የሚያደርገውን መደጋገፍ ሊደነቅ የሚገባው ነው ሲሉም አስምረውበታል።
ምናልባትም መንግስት ነኝ ብሎ ራሱን የሚጠራው አካል በማሰር አሸንፋለሁ የሚል አጀንዳ ቢኖረውም ነገር ግን በየማጎሪያ ስፍራው ዜጎች እርስ በርሳቸው እንዲቀራረቡና አንዱ ለአንዱ እንዲቆም ብሎም ኢትዮጵያዊነታቸውን እንዲያጸኑ አድርጓቸዋል ሲሉ በአይናቸው ያዩትን ምስክርነት ተናግረዋል።