(ኢትዮ 360-ሚያዚያ 25/2015)በአዲስ አበባ ከተማ ተጽእኖ ፈጣሪ ናቸው የሚባሉ የአማራ ተወላጅ መምህራንን ለማፈን አዲስ መመሪያ መውረዱን የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
ሰሞኑን ከየቦታው የእጅ ስልካቸው ጭምር እየተቀማ ወደ አልታወቀ ስፍራ የተወሰዱ መምህራንና በከተማዋ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ የአማራ ተወላጆች መኖራቸውን ያነሳሉ።
ሰሞኑ ታፍነው ከተወሰዱት መካከል ከባድ ድብደባና ማንገላታት ተፈጽሞባቸው ከታፈኑበት የተለቀቁት ደግሞ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ቤታቸው ለባለጊዜዎች ተሰቶ የእነሱ ንብረትና ልጆቻቸውን አደባባይ ተጥለው ማግኘታቸውንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
በየቀበሌው የሚሰሩና በቢሮ ደረጃ ያሉ ሀላፊዎች የአማራ ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ የእጅ ስላካቸውን ተነጥቀው ወዳልታወቀ ስፍራ እየተደበደቡ ከተወሰዱ በኋላ እስካሁን የትእንደደረሱ አለመታወቁንም ያነሳሉ።
በተለይ በአማራ ክልል ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ከታወጀ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄደው አይን ያወጣ አፈና ተጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉ ምንቾቹ ተናግረዋል።
በትንሹ ይላሉ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ20ሺ በላይ የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች በዚሁ ጨካኝ ስርአት መታፈናቸውን ነው የተናገሩት።
በዚህ እስር ውስጥ ደግሞ ከአማራው ጋር ወግናችኋል የተለየ ቅርርብ አላችሁ በሚል ብቻ አብረው የታፈኑ የአዲስ አበባና የደቡብ ክልል ተወላጅ ወጣቶች እንደሚገኙበትም ነው ያስቀመጡት።
ከየአካባቢው የሚታፈንውን ወጣት ለማጎር ደግሞ በከተማዋ የግለሰብ ቤቶች ሁሉ ሳይቀሩ ወደ እስር ቤትነት ተቀይረዋል ብለዋል።
በተለይ በከተማ በቀ ስራ የተሰማሩ ወጣቶች፣ሊስትሮዎች፣ቡና በማፍላት የሚተዳደሩ ሴቶችና ሌሎችም የዚሁ አፋኝ ቡድን ሰለባ መሆናቸውን ያስቀምጣሉ።
ሰሞኑን ይላሉ አያት አደባባይ አካባቢ ለአካል ጉዳተኞች የስራ ፈጠራ በሚል የሰጧቸውን ቦታ ከነንብረቱ ያፈራረሰው አካል ሁለት አካል ጉዳተኞችንም አፍኖ መውሰዱን ነው የኢትዮ 360 ምንጮች የተናገሩት።
በዚሁ ቡድን የሚታፈነው ወጣት በሚያርፍበት ቦታ የሚሰጠው ነገር ቢኖር በቀን አንዲት ኮቾሮ ሲሆን ውሃም ሆነ ወደ ውጪ ወቶ አየር እንዲያገኝ የሚደረግበት ምንም አይነት አጋጣሚ አለመኖሩንም ነው ከእስር የተፈቱት የአማራ ተወላጆች የሚናገሩት።
በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ፣የአዲስ አበባና የደቡብ ክልል ወጣቶችን ያሰረው አካል ዛሬም አፈናውን ቀጥሏል ሲሉ የአይን እማኞች ለኢትዮ 360 ገልጸዋል።