ነሀሴ 9/2015
በአሸባሪነት የተፈረጁ ጋዜጠኞች ላይ ንብረት ላይ እግድ ሊጣል መሆኑን ምንጮች ገለጹ።
ለሰው በላው ስርአት አስጊ ናቸው የተባሉና በአሸባሪነት የተፈረጁ ጋዜጠኞች፣የማህበረሰብ አንቂዎችና ሌሎች ግለሰቦች ንብረት ላይ እግድ ሊጣል መሆኑን የኢትዮ 360 የውስጥ ምንጮች ገለጹ።
በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት የሃብት ምርመራና ማስተዳደር ዋና ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጸሃይ ሃይሉ በተጻፈ ደብዳቤ ትእዛዝ መውረዱንም ይናገራሉ።
በዚህ ደብዳቤ ላይ የ59 ሰዎች ስም ዝርዝር የሰፈረ ሲኖር ከነዚህ ውስጥ ደግሞ የነመምህርት መስከረም አበራ፣የነ ደራሲ ሲሳይ አውግቸው፣የነ ሞላልኝ ሲሳይና በአሸባሪነት ተፈርጀዋል የተባሉት የኢትዮ 360 አባላት ስም በዝርዝሩ ውስጥ ሰፍሮ እንደሚገኝ ምንጮቹ በማስረጃ በማስደገፍ ያሳያሉ።
ለስርአቱ ስጋት በመሆናቸው ብሎም ሙሉ በሙሉ የአማራ ተወላጆች የሆኑትና ስማቸው የሰፈረውን ሰዎች ስም ዝርዝር ያወጣው አካል በነዚህ ሰዎች ስም ወይንም በቡድን የተያዘ ንብረት ካለ ይጣራልኝ ሲል በደብዳቤው መላኩን ይናገራሉ።
ኢትዮ 360 እጅ በገባው በዚህ ደብዳቤ ላይም በግለሰቦቹ ስም በግልም ሆነ በጋራ ወይንም በማህበር በመደራጀት የንግድ ድርጅት ማቋቋሚያ የሚሆን ቦታ ወይም የመኖሪያ ቤት መስሪያ የሚሆን ቦታ ካላ እንዲጣራ የሚለው በደብዳቤው ላይ የሰፈር መሆኑን ያነሳሉ።
በምሪት፣በሊዝ፣በግዥ ወይም በማህበር ተደራጅተው የተመሩ ስለመሆኑ፣በስማቸው የሚገኝ የመኖርያ ቤትም ሆነ የድርጅት ህንጻ ስለመኖርና ያለመኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ ንብረቱ የሚገኝበት ወረዳ፣ ቀበሌ፣የቤት ቁጥርና ቀበሌ ወይንም የመንገድ ስም ተለይቶ ይቅረብ ሲልም ትእዛዝ መስጠቱን ተናግረዋል።
በደብዳቤው ላይ ቤትና ንብረት አላቸው የሚባሉ ግለሰቦች በጥቁር ቀለም ምልክት እንዲደረግበት ሆኗል ሲሉም የኢትዮ 360 የውስጥ ምንጮች ተናግረዋል።
Comentários