በደቡብ ክልል አዲስ ተመሰረተ በተባለው ክልል ውስጥ ያሉው የዶንጋ ማህበረሰብ መብቱን በመጠየቁ ብቻ እየተሳደደና እየታሰረ ነው ሲሉ የማህበረሰቡ አባላት ለኢትዮ 360 ገለጹ።
አዲስ ተቋቋመ በተባለውና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በተቃወመው ክልል ውስጥ ዛሬ ላይ በርካታ ወጣቶች በገፍ እየታሰሩ መሆኑን አስቀምጠዋል።
የተወሰኑ አካባቢዎች ሲያነሱት የነበረው ጥያቄ ተመልሶልናል ያሉ የህብረተሰቡ ክፍሎች ዝምታን ሲመርጡ የዶንጋ ህዝብ ግን አሁንም ጥያቄውን የሚመልስለት አቶ እየተባረረና እየታፈነ ነው ብለዋል ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃቸው ላይ።
የዶንጋ ህዝብ ጥያቄው ሊመለስለት ያልቻለው ደግሞ መጤ የአማራ ስብስብ ናችሁ በሚል መሆኑንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ይሄንን ስም የሚያሰጠውና ወጣቱንና የመብት ጥያቄ የሚያነሳውን ሁሉ እያሳሰረ ያለው ደግሞ የከንባታ ጠምባሮ አመራሮች መሆናቸውንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
እየታፈኑ ከሚታሰሩ መካከል ከፍተኛ ድብደባ እየተፈጸመባቸው ያሉት ወጣቶች ህክምና የሚሰጣቸው አተው በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰቃዩ መሆኑን አመልክተዋል።
ሀደሮ፣ጡንጦና ማዞሪያ ደግሞ በከባዱ የንጹሃን ዜጎች አፈናና ድብደባ የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
እስካሁን ለጥያቄው ምላሽ ያላገኘውን የዶንጋን ህዝብ አብሮ በመቆም እያገዙ ላሉት የሀዲያ፣የወላይታና የአማራ ህዝቦችም ያላቸውን ትልቅ አክብሮት ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ አስፍረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማሮ ኮሬ ዞን ያለው የዜጎች አያያዝ ስርዓት እጅግ የሚያሳዝንና ዘግናኝ ድርጊቶች የሚፈጸምበት ሆኗል ሲሉ ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ አስታወቁ።
በነዋሪው ላይ ያለምንም ምክንያት የሚፈጸመው የከፋ ድብደባ በቃላት የሚገለጽ አይደለም ሲሉ አሳዛኙን ገጽታ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ አስፍረውታል።
ከየመንደሩና ከየቤቱ ታፍኖ የሚወሰደውም ነዋሪ ቁጥር ከፍተኛ ነው ሲሉ ይገልጹታል።
ከየአካባቢው የሚታፈነው ወጣት ደግሞ የሚታጎረው 3 በ4 በሆነ ክፍል ውስጥ ሆኖ በዛ ውስጥ ደግሞ ከ50- እስከ 60 የሚሆኑ ንጹሃን ዜጎች በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ እንዲታፈኑ ሆነዋል ይላሉ።
ማጎሪያ ስፍራው ከመጨናነቁ የተነሳ ከታሳሪዎች የሚወበጣው ላብ ወደ ጣሪያ ላይ ደርሶ እንደዝናብ ወደ ታች ይፈሳል ሲሉ በመረጃቸው ላይ አስፍረዋል።
ከደርባና ጉሙሬ ቀበሌዎች ታፍነው የመጡ ንጹሃን ዜጎችም አንድ ክፍል ውስጥ ታጉረው እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በአበዛኛው ከየአካባቢው ታፍነው የሚወሰዱ ንጹሃን ዜጎች አብዛኞቹ የት እንደሚወሰዱ አይታወቅም የሚሉት ነዋሪዎቹ የታሰሩበት ቦታ የሚታወቀውም ቢሆን ጥፋታቸው ታውቆ ፍርድ ቤት ቀርበው ጉድያቸው እንዲታይ አይደረግም ብለዋል።
ከዛም አልፎ ንጹሃን ዜጎቹ ከየትኛውም ወገናቸው ጋር እንዳይገናኙ ተደርገው መታሰራቸው ደግሞ መከራቸውን የከፋ አድርጎታል ሲሉ ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ ገልጸዋል፣