የባህርዳር ከተማ ለሊቱን ሙሉ በከባድ መሳሪያ ሲደብደብ ማደሩን ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 ገለጹ።
የአማራ ህዝባዊ ሃይሉ ደግሞ የሳባታሚት ማረሚያ ቤትን ሰብሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የፋኖ፣የልዩ ሃይል፣የጦር መኮንኖችንና ሌሎችን ነጻ ማውጣታቸውንም ይናገራሉ።
ይሄን እያደረጉ ባለበት ሰአት ደግሞ መኮድና ቀበሌ 14 አካባቢ ከባድ የሆነ የከባድ መሳሪያ ተኩስ እንደነበርም ተናግረዋል።
ቤተክርስቲያን የሚሄድ ምእመናን ሳይቀር በዚሁ ገዳይ ቡድን እየተመቱ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ እየተደረገ ያለው ነገር ከተማዋን የማውደም ስራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በአማራ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እየተፈጸመ መሆኑንም ሁሉም እንዲያቀው መደረግ አለበት ባይ ናቸው።
ሞርተርና ታንክን ጨምሮ ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችም ወደ ህዝቡና ወደ ከተማው በመወንጨፍ ላይ ናቸው ሲሉም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
የብአዴኑ አመራር ከተማዋን አስቀድሞ ዘርፎ ነው የሄደው የሚሉት ነዋሪዎቹ ወደ ክልሉ የገባው ሃይል ደግሞ አካባቢውን እያወደመ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
ሁሉም አማራ ነኝ የሚል በመላው አላም የሚኖር በሙሉ በዚህ ትግል ውስጥ ጩህቱን ሊያሰማ ይገባል ሲሉ ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 ገልጸዋል።
ባህርዳር በቀበሌ14፣ ድባጤ፣ ገጠርመንገድ ብዙሐን መገናኛና በመኮድ አካባቢ ህዝባዊ ሃይሉ መብረቃዊ የሆነ ጥቃት በገዳዩ ብዱን ላይ ማድረሱንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ከለሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮም ከባድ ውጊያ እያካሄደ ነው የሚሉት ምንጮቹ በዚህ ደግሞ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ እንዲዳከም አድርጎታል ብለዋል።
በዚህ የተዳከመው ስብስብ የኮማንዶ ሃይልን አምጥቶ በውጊያው ከመጠቀሙም በላይ ከባድ መሳሪያዎችን በንጹሃን ቤት ላይ ሲተኩስ ማደሩንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።