የሐዋሳ ከተማ ከንቲባን አንስቶ ለስርአቱ ታዛዥ የሆነ ሃይልን ለመሾም የሚደረገው ግብግብ ከፍተኛ ተቃውሞ ማስነሳቱን የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
ይሄ ሁሉ ግብግብና ውዝግብ ደግሞ የተነሳው በዋናነት የሌላ ጎሳ አባልትን ለመሾም ነው ሲሉም ምንጮቹ ተናግረዋል።
ይህ የሆነው ደግሞ የከተማው አካባቢ ነዋሪዎች "በሹመት ላይ የእኛ ኮታ ያንሳል።" የሚል ጥያቄ በማንሳታቸውና በክልሉ አመራርም በኩል ጥያቄው ተገቢ ነው በሚል የተሰጠው ምላሽ የልብ ልብ በመስጠቱ ነው ብለዋል።
ይሄ ሁሉ ውዝግብ ባለበትና ነገሮች አቅጣጫ ሊስቱ ባሉበት ሰአት ደግሞ የሲዳም ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ለከፍተኛ ህክምና በሚል ወደ ዱባይ ማቅናቱን ተናግረዋል።
እንደ መረጃው ከሆነ ርዕሰ መስተዳድሩን ለማሳከም በሚል በከፍተኛ ባለሀብቶች ኮሚቴ ተቋቁሞ ገንዘብ ሲሰበሰብ መቆየቱንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ይሁን እንጂ አንድ የመንግሥት የሥራ ኃላፊ ህመም ሲያጋጥመው ከመንግሥት ካዝና በማውጣት በየትኛው እርከን ማሳከም እንደሚቻል በአዋጅ የተደነገገ አንቀጽ መኖሩን ያነሳሉ።
ነገር ግን ነጋዴው እያዋጣ የነበረው ለታይታና ለእጅ መንሻ እንጂ በትክክል ከሃዘኔታ የመነጨ አይደለም ሲሉ በክልሉ ያለውን የእከከኝ ልከክልህ ፖለቲካን አካሄድ አመልክተዋል።