በጎንደር ገዳዩ ቡድን በንጹሃን ዜጎች ላይ ከፈጸመው ጥቃት ጋር ተያይዞ በተባራሪ ጥይት ተመተው ሆስፒታል የገቡ ታዳጊዎችና ህጻናትን ከጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል በማውጣት በአደባባይ እንደረሸናቸው የህዝባዊ ሃይሉ አባላት ለኢትዮ 360 ገለጹ።
እነዚህ ሕጻናትና ታዳጊዎች ከተኙበት የእራጅና የኦፕሬሽን ክፍ በማውጣት ከረሸኗቸው መካከል ደግሞ እድሜያቸው ከ14 አመት በታች የሆኑ ህጻናት እንዳሉበትም ተናግረዋል።
በቀበሌ 18 አካባቢ የሚገኘው አይቤክስ የግል ሆስፒታልም ለህዝባዊ ሃይሉ አባላት ህክምና ሰታችኋል በሚል የላብራቶሪና የኦፕሬሽን ክፍሉን ሙሉ በሙሉ ማውደማቸውን አባላቱ ገልጸዋል።
የፋኖ ጌታሰው በሬ ቤተሰብ በሆነው ልደታ ሆቴል በመግባት ንብረት አውድመዋል፣ ካልሲ ሳይቀር ተራ የሚባል ስርቆት ፈጽመዋል ብለዋል።
ማክሰኝት ደንገጽ የሚባል ቦታ ላይ አንድ ሻለቃ ሃይሉ ሙሉ በሙሉ የተደመሰሰበት ገዳይ ቡድን ቤት ለቤት እየገባ ወደ አደባባይ የወሰዳቸውን ትልልቅ ሰዎች በአደባባይ መረሸኑንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ከተገደሉት አብዛኞቹ ደግሞ ከ55 አመት በላይ የሆኑና በእድሜ የገፉ ሰዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ቤዛዊት ማርያም ቤተክርስቲያንን በመሳለም ላይ በነበሩ ንጹሃን ዜጎች ላይ ይሄው ገዳይ ቡድን በከፈተው ተኩስ በትንሹ ከአራት በላይ ልጃገረዶችን ገሏል፣ቁጥራቸው ባልታወቁ ሰዎች ላይ ጭፍጨፋ አካሂደዋል ብለዋል።
ገዳይ ቡድኑ ለዚህ ጭፍጨፋ ምክንያት ያደረገው የህዝባዊ ሃይሉን አባል ቀብር ላይ ተገኝታችኋል በሚል መሆኑንም አባላቱ ለኢትዮ 360 ገልጸዋል።