በምስራቅ ጎጃም እናርጅ እናውጋ ወረዳ የደብረወርቅ ከተማን ለማስከፈት ተኩስ የከፈተው የኦህዴዱ መከላከያ ሃይል አንድ ሴት ገሎ በርካቶችን ማቁሰሉን የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
ይህው ሃይል ከወረዳው ፖሊስ ጋር በመተባበር ለወረዳው ጤና ጣቢያ አገልግሎት የሚውሉ አንቡላንሶችን ለመጠቀም የአንቡላንሶችን ሹፌሮች መሳሪያ በመደቀንና በማስገደድ ከየቤታቸው አፍኖ እንደወሰዳቸውም ይናገራሉ።
በወረዳው ያሉ ሁሉንም አንቡላሶች ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲወሰዱ ማድረጉንም ነው ምንጮቹ ያመለከቱት።
እነዚህን አምቡላንሶች በአንድ ላይ ተሰባስበው የተወሰዱት ለሌላ ጉዳይ ሳይሆን በንጹሃን ላይ ጥቃት ለመፈጸሚያ ብቻ ነው ሲሉ እየተሰራ ያለውን ወንጀል አጋልጠዋል።
በአምቡላንስ ሲንቀሳቀሱ የፋኖ ህዝባዊ ሃይልም ሆነ ማህበረተሰቡ አያውቅም ስለዚህም በቀላሉ ጥቃት ለመፈጸም ያስችለናል የሚለው ደግሞ በአካባቢው ፖሊስ ጭምር ምክር የተሰጠበው ነው ሲሉ የታሰበውን ተንኮል ያጋልጣሉ።
የፋኖ ህዝባዊ ሃይልን ፊት ለፊት መግጠም ያልቻለው የኦህዴዱ ስብስብና የአካባቢው ሆድ አደር ካድሬ ትናንት በሽማግሌ ሰላም እንደወረደ አስመስለው ፋኖ አዱኛው ፍቃዱን ሲያስበሉ አሁን ደግሞ በአንቡላስ ወላድ ወይንም ህመምተኛ መስለው የደብረወርቅ ፋኖን ለማጥቃት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል ብለዋል።
በምስራቅ ጎጃም ደብረወርቅ ከተማ እና አካባቢው ላይ የኦህዴድ ሃይል በንፁሀን አርሶ አደሮች እና ህፃናት ላይ የጀመረውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች እየፈጸመው ነው ሲሉ የኢትዮ 360 ምንጮች ተናግረዋል።