በአፋር ክልል የብልጽግናውን አስተዳደር ይቃወማሉ የተባሉ ወጣቶች ሁሉ በገፍ እየታሰሩ መሆኑን የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
በማህበራዊ ድረገጽ ላይ ስርአቱን የሚቃወሙ ጽሁፎችን ሼርና ላይክ የሚያደርጉ ሁሉ የዚህ አፈና ሰለባ እየሆኑ ነው ብለዋል።
እስካሁንም ቀአስ መሃመድ፣አሊ ሁሴን፣ሐሰን ሁሴን፣መሃመድ ሐሰንና በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች በተለያዩ እስር ቤቶች ታፍነው እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ክልሉን እመራለሁ የሚለው አካል እስከ ታችኛው ካድሬ በመተባበር በዋናነት እነዚህን ወጣቶች አሳሪና አሳሳሪ መሆኑን ይናገራሉ።
ሰሞኑን በተከታታይ በአፋር ንጹሃን ዜጎች ላይ የኦህዴዱ መከላከያ ሃይል የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ስለተገደሉት ንጹሃን ወገኞቻቸው የጻፉም ሆኑን ጽሁፉን ለሌላ ያጋሩ በሙሉ በዚሁ አካል እየተሳደዱና እየታፈኑ መሆኑን ይናገራሉ።
አፈናና እስሩ በየቀኑና በየሰአቱ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ምን ያህል ወጣቶች እነዳፈኑ ማወቅ እንዳልተቻለም ምንጮቹ አመልክተዋል።
የእያንዳንዱ የመንግስት ሰራተኛ ስልክ በመጥለፍ ጭምር ብርበራ የሚያካሂደው የክልሉ አስተዳደር በየመንገዱ የሚያገኘውን ወጣትም ስልክ ካልፈተሽኩ በሚል ስራ በዝቶበታል ብለዋል።
በአፋር ክልል ያለው አፈናና ማሳደድ ከኑሮው ጋር ተጨምሮ የህዝቡን መከራ አብዝቶታል ብለዋል የኢትዮ 360 ምንጮች።
