ኢትዮ 360 - ነሐሴ 10/2015) በባህርዳርና አካባቢው የሚገኙ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች አላስፈላጊ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ነው።
- Ethio 360 Media 2
- Aug 16, 2023
- 1 min read
በባህርዳርና አካባቢው የሚገኙ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ህዝባዊ ሃይሉ ከከተማው መወጣቱን ተከትሎ አላስፈላጊ የሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ህብረተሰቡን እያሰቃዩት ነው ሲሉ የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
እነዚህ ስግብግብ ነጋዴዎች የህዝባዊ ሃይሉን የህልውና ትግል የሃብት ማካበቺያ እያደረጉት ነው ይላሉ።
የዋጋ ንረቱን በእጥፍ ያሳደገው ይሄው ስብስብ የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ 70 ብር ነበር ዛሬ ላይ አንድ ኪሎ የሽንኩርት ዋጋ 140 ብር እንዲገባ ሲያደርግ በአንድ ሊትር ዘይት ዋጋ ላይ ደግሞ የ500 ብር ጭማሪ አድርገዋል ሲሉ በማሳያነት ያቀርባሉ።
በአንጻሩ ደግሞ የህዝባዊ ሃይሉ በተቆጣጠረባቸው አካባቢዎች አላግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎችን መደብር በማሸግ ማህበረሰቡን ከስቃይ እየታደገው ነው ይላሉ።
ህብረተሰቡን ይቅርታ የጠየቁ ነጋዴዎች ደግሞ መደብራቸው ተከፍቶላቸው ወደ ስራ መመለሳቸውንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባህርዳርን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ያለው አፈና አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮ 360 ምንጮች ገልጸዋል።
በየመንገዱ የሚገኝ ብቻ ሳይሆን ቤት ለቤት በሚደረገው አፋና በየቦታው የሚገኝ ወጣት ይታሰራል ለአቅመ አዳም የደረሱ ሴቶች በዚሁ ግፈኛ ቡድን ይደፈራሉ ብለዋል።
ከዛም አልፎ በየቤቱ የሚደረገው ዝርፊያም አይን ባወጣ መልኩ ቀጥሏል ሲሉ የኢትዮ 360 ምንጮች አስታወቁ።