የአማራ ወጣቶች ማህበር የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ምክትል ሊቀ መንበር በኦህዴዱ ሃይል መታፈኑን ቤተሰቦቹ ለኢትዮ 360 ገለጹ።
ምክትል ሊቀመንበሩ አበባው ማሙዬ በዚሁ ቡድን የታፈነው ቤተሰብ ጥየቃ ወደ ደብረብርሃን በሄበደበት መሆኑንም ይናገራሉ።
ወጣት አበባው ማሙዬ በዚሁ ሃይል ታፍኖ ከተወሰደም በኋላ እስካሁን የት እንደገባ እንደማያውቁም ነው ቤተሰቦቹ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ያስታወቁት።
ማህበሩ በቅርቡ በኦህዴዱ ስርአት ጥርስ ከተነከሰባቸው ተቋማት ብቻ ሳይሆን የሒሳብ አካውንቱ ሁሉ እንዲታገድበት መደረጉ ይታወሳል።
ያንን ተከትሎም አመራሩንና አባላቱን የማሳደዱን ዘመቻ ያጠናከረው የኦህዴዱ ስብስብ አመራሩን በአደባባይ ወደማፈን ተሸጋግሯል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በአዲስ አበባ ከተማ ከየቦታው የሚታፈኑ የአማራ ተወላጆች ቁጥርን መናገር የማይቻልበት ደረጃ ደርሷል ሲሉ የአይን እማኞች ለኢትዮ 360 ገለጹ።
አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያን ጨምሮ በየቦታው የታጎሩ የአማራ ተወላጆች ከብዛታቸው የተነሳ ቤቱ ይቁጠራቸው ሲሉ ነው ሁኔታን የገለጹት።
ከነዚህ ከታፈኑት መካከልም የአንድ የቅርብ ወዳጃቸውን ጉዳይ ለመከታተል መሞከራቸውንም ያነሳሉ።
ሀና ማሪያም አካባቢ የሚኖረው ወዳጃቸው የታፈነው ከለሊቱ 9 ሰአት ወደ 20 በሚሆኑ ፖሊሶች መሆኑንም ገልጸዋል።
በየቦታው ወዳጃቸውን ለመፈለግ በሄዱበት ከደረሰባቸው እንግልት ሌላ ያገኙት አንዳችም መፍትሄ እንደሌለ ያስቀምጣሉ።
ምላሽ የሚሰጥ አካል መጥፋቱ ብቻ ሳይሆን የተገኙት ሰዎችም ቢሆኑ ከምላሹ ይልቅ ወደ ማስፈራራትና ዛቻ የሚያዘነብሉ ናቸው ሲሉም ሁኔታውን አስቀምጠዋል።
Comments