በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ራሱን አጥፍቷል በሚል የተሳሳተ መረጃ ሲወጣበት የነበረው ተማሪ አባባው ስንሻው አራት ቦታ በስለት መወጋቱን የኢትዮ 360 የዩኒቨርስቲው ምንጮች ገለጹ።
ከአንድ ቀን በፊት ኢትዮ 360 ባወጣው መረጃ ዩኒቨርስቲው ተማሪ አበባው ራሱን ገሎ ነው ሲል ያወጣው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን ማጋለጡ ይታወሳል።
ነገር ግን ተማሪ አበባው ራሱን ገሎ ሳይሆን ሆን ተብሎ መገደሉንና ከተገደለም በኋላ ከዶርም ውጪ በሚገኘውና ቆርቆሮ በቆርቆሮ በተሰራው መጸዳጃ ቤት እራሱን አጥፍቶ እንዲገኝ መደረጉን ይፋ አድርጓል።
አሁንም የኢትዮ 360 የዩኒቨርስቲው የውስጥ ምንጮች ተማሪ አበባው አራት ቦታ በጩቤ መወጋቱንና ሰውነቱ በሙሉ ደምበደም ሆኖ መታየቱንም አጋልጠዋል።
ተማሪ አበባው በስለት የተወጋው አንገቱና ጎኑ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አሁንም የተማሪውን ጉዳይ በትክክል ማጣራት ያልፈለገው የዩኒቨርስቲው አስተዳደር በኦህዴዱ የጸጥታ ሃይል የአማራ ተማሪዋችን በሌሊት እያሳፈነና እያስደበደበ ነው።
ትናንት ከምሽቱ 3:00 ሰአት አካባቢ ግቢው ውስጥ ካለው ሀበሻ ካፌ ራት አሰርተው ይዘው ሲመጡ የተደበደቡ ሴት ተማሪዋች ሆስፒታል መግባታቸውንም ነው የዩኒቨርስቲው የውስጥ ምንጮች የሚናገሩት።
በድብደባ ብዛት መንቀሳቀስ ያልቻሉ ተማሪዎች ያለምንም ህክምና በዶርማቸው ተኝተው እንደሚገኙም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ወደ ቤተመጻህፍት ሲሄዱም ሆነ በየዶርማቸው ያሉ የአማራ ተወላጆች ሁሉ በዚሁ ሃይል የሚደርስባቸው ማሳደድና ድብደባ አሁንም መቀጠሉን ምንጮቹ ተናግረዋል።