በምሥራቅ ሐረርጌ በሜታ ወረዳ፣ ጨለንቆ አካባቢ ሰሞኑን ከመከላከያ ሃይል ጋር ጦርነት የገጠመው የኦነግ ቡድን አካባቢውን መውረሩ ማህበረሰቡን ከባድ ስጋት ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል ሲሉ ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 ገለጹ።
በአቦቴ ጨለንቆ ሰሞኑን በመከላከያ ሰራዊት እና በኦነግ ሸኔ ሰራዊት መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ አስፍረዋል።
ከተከፈተው ጦርነት ጋር ተያይዞ ከአካባቢው የሸሸው የኦነግ ገዳይ ቡድን በጀማ አካባቢና ከጀማ ማዶ ሸንበቆ በሚባለው ቦታ እንዲሁም ከጀማ ወዲህ ደራ ውስጥ ቀሪሶ በሚባል ቦታ ድንኳን ተክሎ መቀመጡን ይናገራሉ።
በመንቃታ እና በባቡ በረሀ አካባቢ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኦነግ ሰራዊት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ህብረተሰቡን ሰላም ነስቶታል ባይ ናቸው።
ይሄው ገዳይ ቡድን ሰሞኑን ጃርሶ ዱለታ ላይ ከ700 በላይ አዲስ ምልምል ሃይል ማስመረቁን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ ይሄው ሃይል የጀማን ወንዝ ተከትሎ ወደ ደራ መግባቱንም ያነሳሉ።
ይሄ ገዳይ ቡድን በዚህ መልኩ አካባቢውን ወሮ ባለበት ሰአት ደግሞ የደራ ወረዳ አንዳንድ አመራር የደራ ሚኒሻን የተለያዩ ፈረጃዎችን በመስጠት እያሸማቀቀው ነው ብለዋል።
ይሄን የሚያደርገው ደግሞ ሚሊሻው አብዛኛው ስብስብ በፋኖ ህዝባዊ ሃይል የተሞላ ነው በሚል የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ጭምር በዚሁ ገዳይ ቡድን ለማስመታት እየጣረ ነው ብለዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የታሰሩ የሚሊሻ አባላት መኖራቸውን ሳይጠቁሙ አላለፉም።
አሁንም ይላሉ ነዋሪዎቹ በተለይ በደራ አካባቢ ያለው የዚሁ ገዳይ ቡድንና የወረዳው አመራሮች በጋራ ህብረተሰቡ ላይ ሊያደርሱት ያሰቡት ጥቃት በመኖሩ ሌላው አካል ሊደርስላቸው ይገባል ሲሉ ስጋታቸውንም አስቀምጠዋል።
አሁን እየሄዱበት ካለው ርቀት አኳያ አስቸኳይ ምላሽ የሚሰጥ ወገን ካልደረሰ አደጋው የከፋ ነው ሲሉ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
Comments