በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶችንና ቤቶችን ለመውረስ የሚያስችል አዲስ መመሪያ ተግባራዊ መሆኑን የኢትዮ 360 የውስጥ ምንጮች ገለጹ።
ለዚህ ማስፈጸሚያ ደግሞ የጋራ መኖሪያ ቤት ባለቤቶችም ሆኑ የግል መኖሪያ ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የተተመነላቸውን ግብር እስከ ሰኔ 30 መክፈል አለባቸው የሚል አስገዳጅ መመሪያ ወርዷል ይላሉ።
ኢትዮ 360 በቅርቡ ባወጣው መረጃው የጋራ መኖሪያ ቤቶችና የግል ቤቶች የጣራና ግርግዳ ግብር እንዲከፍሉ መወሰኑን ይፋ አድርጎ ነበር።
የራይድ አሽከርካሪዎች ደግሞ ከ70 እስከ 80ሺ ብር ግብር ክፈሉ ሲባሉ የግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ ክፍያቸው መቶ በመቶ ጭማሪ እንዲደረግበት መወሰኑንም በመረጃው ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
እናም አሁን ላይ ሁሉንም ካልጠቀለልኩ የሚለው የኦህዴዱ ኦነግ ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤት ባለቤቶችም ሆኑ የግል መኖሪያ ቤት ያላቸው የተቀመጠላቸውን የግብር መጠን እስከ ሰኔ 30 እንዲከፍሉ የሚል መመሪያ አወርዷል ብለዋል።
እንደማሳያ በ60 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባ የጋራ መኖሪያ ባላቤት 8ሺ 38 ብር ክፈል የሚል ታሪፍ ወቶለታል ብለዋል።
የግል መኖሪያ ቤት ባለቤት ደግሞ ከ30ሺ እስከ 40ሺ ብር እስከ ሰኔ 30 መክፈል አለብህ ተብሏል ይላሉ።
ይሄን መክፈል ያልቻለ የከተማዋ ነዋሪ አይኑ እያየ ቤቱ ይወረሳል ማለት ነው ሲሉ የውስጥ ምንጮቹ ይናገራሉ።
ህብረተሰቡ ላይ አይን ያወጣ ዝርፊያ ለመፈጸም ሁሉም አሰፍስፎ የተነሳው እስከ ሰኔ 30 እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሶስት ሚሊዮን ብር በነፍስ ወከፍ እንዲያስገባ ጥብቅ መመሪያ በመውረዱ ነው ብለዋል።
ይሄንን ለማፈጸም ደግሞ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች በሁለት ሽፍት ተከፍለው እንዲሰሩ መደረጋቸውንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
የመጀመሪያ ሽፍት ጠዋት 12 ሰአት ገብቶ ቀን 9 ሰአት ላይ ሲያጠናቅቅ የቀኑ ሽፍት ደግሞ ከቀኑ 9 ሰአት እስከ ምሽቱ 4 ድረስ የሚቆይ መሆኑንም የኢትዮ 360 የውስጥ ምንጮች ተናግረዋል።
Kommentare