በትግራይ ክልል የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ቅስቀሳ ላይ የነበሩ ስድስት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ዛሬ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
ይሄንን ተከትሎም በከተማው ከባድ ውጥረት መንገሱን ነው ምንጮቹ የሚናገሩት።
ከዚህ እስር በፊት የፓርቲዎቹ አባላት አስቀድመው በሰጡት መግለጫ ላይ እንዲህ አይነቱ ችግር እንደሚገጥም ጠቆም ለማድረግ መሞከራቸውን ያነሳሉ።
ፓርቲዎቹ በመግለጫቸውም ክልሉን በጊዜያዊነት የሚያስተዳድረው አካል ሰልፉን ሊያደናቅፍ ቢሞክር እንኳን እነሱ ሊያካሂዱት ያሰቡት ሰልፍ እንደማይቀር በግልጽ ማስቀመጣቸውን ይናገራሉ።
ዛሬ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከልና ሰልፉን በመጭው ሃሙስ ለማካሄድ አስበው የነበሩት ፓርቲዎች ሳልሳይ ወያነ፣ የትግራይ ነጻነት ፓርቲ እና ባይቶና መሆናቸውን አንስተዋል።
የከተማዋ አስተዳደርም ፓርቲዎቹ ሊያካሂዱ ላሰቡት ሰላማዊ ሰፍል ፍቃድ አለመስጠቱንም ጠቁመዋል።
በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ሕወሃት-መር የሆነው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፈርሶ በሕዝባዊ አስተዳደር እንዲተካና የትግራይ "ሉዓላዊ ግዛቶች" እንዲመለሱ የሚጠይቁና ሌሎች መፈክሮችን ለማሰማት በዝግጅት ላይ እንደነበሩም አመልክተዋል
Comments