የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ኢንሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲል አስማማውና የኪነጥበብ ባለሙያው አርቲስት ዱባለ መላክን ጨምሮ ከየተገኙበት የታፈኑ ንጹሃን ዜጎች ያሉበትን ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ መቀጠሉን የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲል አስማማው ቅዳሜ ነሀሴ ሃያ ቀን ፒያሳ ከሚገኘው ቢሮው ሲወጣ ሲከታተሉት በነበሩት አፋኝ ቡድኖች መያዙን ይናገራሉ።
እስካለፈ ማክሰኞችም ሜክሲኮ ገነት ሆቴል አጠገብ በሚገኘው ፌደራል ፖሊስ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ ወደ አዋሽ አርባ ተወሰደ መባሉንና ነገር ግን ቤተሰቦቹ ቢጠይቁም ተወሰደ በተባለበት ቦታ አለማግኘታቸውን አመልክተዋል።
በተመሳሳይም አርቲስት ዱባለ መላክ በደሴ ከተማ ከታፈነ በኋላ ወደ መሮህ ግቢ ተወሰደ ይባል እንጂ ቤተሰቦቹ ግን እስካሁን ድረስ ያለበትን ቦታ ማወቅ አልተቻለም ብለዋል።
በሁሉም አካባቢዎች እየታፈኑ ያሉ ዜጎችን ማግኘት አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ አካል አለመኖሩ በራሱ ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎታል ብለዋል።
በየማጎሪያ ስፍራው ያሉ ንጹሃን ዜጎች ደግሞ የሚበሉት ምግብም ሆነ የሚጠጡት ውሃ እንዳያገኙ ብሎም እየተሰቃዩ ላሉበት ህመም ምንም አይነት ህክምና እንዳያገኙ በመከልከል ጭምር የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተባባሰ መምጣቱንና በዚህም ህይወታቸው እያለፈ ያሉ ንጹሃን ዜጎች መኖራቸውን ኢትዮ 360 በተደጋጋሚ በመረጃው ሲያወጣ መቆየቱ ይታወሳል።
Comments