አዲስ አበባ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ቀድሞ ይሰሩ የነበረበትን አሰራር ሁሉ እንዲቀይሩ ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን የኢትዮ 360 ምንጮች አስታወቁ።
የግል ትምህርት ቤቶች የተማሪውን ውጤት የሚሞሉበት ካርድም ሆነ ሌላው የሚሰራው በራሳቸው ፖሊሲ መሆኑን ይናገራሉ።
ነገር ግን አሁን ላይ እያንዳንዱ የውጤት መስጫም ሆነ ሌላ የስራ ወረቀቶች አርማቸው ላይ ኦሮምኛ ቋንቋን እንዲያስገቡ ግዴታ ተጥሎባቸዋል ይላሉ።
አሁን ላይ ካርዶቹን እኛ አሳትመን ከምንሰጣችሁ ውጪ ሌላ ካርድ መጠቀም አትችሉም የሚል መመሪያ እንደወረደላቸውም ይናገራሉ።
ነገር ግን በቀድሞ አሰራር የመንግስት ትምህርት ቤቶች በመንግስት ፖሊሲ ሲተዳደሩ የግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ በራሳቸው ፖሊሲ ይተዳደሩ እንደነበር ያነሳሉ።
አሁን ግን ያ ሁሉ ቀርቶ እኛ ያልናችሁን ካልፈጸማችሁ ትምህርት ቤቱን እንዘጋለን ወደ ሚል ማስፈራሪያም መሸጋገራቸውን አስቀምጠዋል።
አሁን ላይ የግል ትምህርት ቤቶች ከመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚለዩት በሚያስቀምጡት ማህተም ብቻ ሆኗል ሲሉ አሳዛኙን አካሄድ ይናገራሉ።
የግል ትምህርት ቤቶችን ፖሊስ ሙሉ በሙሉ የሰረዘው ይሄው ስብስብ በሁሉም ቦታ ላይ በኦሮምኛ ካልጻፋችሁ ማስተማር አትችሉም ወደሚል ደረጃ ተደርሷል ብለዋል።
ከሁሉም አሳዛኙ ነገር ይላሉ የትኛውም የግል ትምህርት ቤት ዝቅተኛ ውጤት ያመጣ ተማሪንም በምንም ሁኔታ መጣል አትችሉም የሚል ውሳኔ እንደተላለፈላቸው ምንጮቹ ገልጸዋል።
የትምህርት ስርአቱን ብቻ ሳይሆን ትውልድ እየገደለ ያለው ይሄው የገዳዮች ስብስብ ምናልባትም አሁን በያዘው አካሄድ ከቀጠለ መጪው ጊዜ ለትምህርት ቤቶችም ሆነ ለተማሪዎች ብሎም ለወላጆች ፈታኝ ሊሆን ይችላል ሲሉም የኢትዮ 360 ምንጮች ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።