በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ያለምንም ማስጠንቀቂያ እንዲፈርስ የተደረገው የመንዲዳ ገበያ ነጋዴዎችና ተገልጋዮች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ለኢትዮ 360 ገለጹ።
የመንዲዳ ገበያ ሲፈርስ ከ20 እና ከ15 አመት በላይ በቦታው ይሰሩ ለነበሩት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ ባልተሰጠበት ሁኔታ ውስጥ ነው ይላሉ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ።
ይሄ ህገወጥ ፈረሳ ሲካሄድ ደግሞ ከጎናቸው ቆሞ ድምጻቸውን ሊያሰማላቸው የሞከረ የብዙሃን መገናኛ አለመኖሩንም ያነሳሉ።
መንዲዳ ትልቅ የገበያ ማእከል እንደሆነ የሚገልጹት ነጋዴዎቹ በተለይ በጨረታ ከአስኮ ጨርታ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የልብስ ጫረታ የሚከናውንበት እንደሆነም ያስቀምጣሉ።
በአንድ ቀን ብቻ እስከ 10,000ሺ የሚደርስ የድሃው ማህበረሰብ ሲገበያይ የሚውልበት የገበያ ማዕከል መሆኑንም በመረጃቸው ጠቁመዋል።
ይሄንን ሁሉ ማገናዘብ ያልቻለው ስርአት ግን የ10,000 ሺ ማህበረሰብ ጉሮሮ ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘግቶታል ሲሉም አስምረውበታል።
በድንገት የንግድ መደብሩ ወደ ፍርስራሽነት እንዲቀየር የተደረገው የንግዱ ማህበረሰብም ሜዳ ላይ ፈሶ ማረፊያ ስፍራ እንኳን አላገኘም ብለዋል።
ከጦርሃይሎች በቅርብ እርቀት ላይ የሚገኘው የገበያ ማእከል በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ነጋዴዎች የሰልባጅ ንግድን በመስራት ሃገራቸውን እንደ ሀገር የሚመጣባት ፈተናና ችግር ከጎንዋ በመቆም በተጠሩበት ሁሉ የበኩላቸውን ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ይናገራሉ።
ይሄ ማህበር ይሄን የሚያደርገው ከተቋቋመት ከ20 አመት በላይ ባሉት ጊዜያቶች ሁሉ ውስጥ መሆኑንም ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ አመልክተዋል።
የመንዲዳ የንግድ ማእከል የአዲስ አበባ ነዋሪ ብቻ የሚነግድባት ሳይሆን ከተለያየ የክልል ከተሞች የሚመጡ ነጋዴዎች የተሰማሩበትም እንደነበር አንስተዋል።
የሚያሳዝነው ይላሉ ይሄ የንግድ ማዕከል ውስጥ ሰሞኑን ቤታቸው ፈርሶባቸው ቢያንስ ትንሽ ሰርተው ለልጆቻቸው ምግብ ለማቅረብ ሲሞክሩ የነበሩ እናቶች ዛሬ ላይ ከነልጆቻቸው ባዶአቸውን እንዲቀሩ ተደርገዋል ብለዋል።
ከ15 ቀን በፊት የምትኖርበት ቤት የፈረሰባትና አሁን ደግሞ የምትሰራበት የንግድ ስፍራ የፈረሰባት እናት ለዚህ ማሳያ ናት ይላሉ።
ያለ አባት ያሳደገቻቸው አራት ልጆቿ ዛሬ ላይ መግቢያም ቤት የሚቀምሱትም አተው ጎዳና ላይ መውደቃቸውን ያነሳሉ።
ሌላውም የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በተመሳሳይ መልኩ በአንድ ጀንበር ከስራቸውም ከኑሯቸውም እንዳይሆኑ ተደርገው መቀጣታቸውን ነው ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ ያመለከቱት።
Comments