በአርሲ ሀገረ ስብከት በአሰላ ከተማ አካባቢ በሚገኘው የዴራ አማኑኤል አጥቢያ ቤተክርስቲያን ላይ የኦነግ ገዳይ ቡድን በፈጸመው ጥቃት አራት የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎችን መግደሉን ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 ገለጹ።
በዚሁ አጥቢያ ቤተክርስቲያንና በአካባቢው ይሄ ቡድን በፈጸመው ጥቃት የቤተክርስቲያኗ አገልጋይ አባቶችን ጨምሮ በቁጥር ያልታወቁ በርካታ የአማራ ተወላጆችን መግደሉን ነው ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ ያሰፈሩት።
በዚሁ ገዳይ ቡድን በግፍ ከተጨፈጨፉት ውጪ ከአካባቢው ታፍነው የተወሰዱ ሰዎች መኖራቸውንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
እንዲህ አይነቱ የግፍ ግድያ በአሰላ ከተማ ገጠራማ ቀበሌዎች ተባብሶ መቀጠሉንም ይናገራሉ።
በአካባቢው ሰሞኑንም ዘርን መሰረት አድርጎ በርካታ የአማራ ተወላጆች መገደላቸው ይናገራሉ።
ከዛም አልፎ ከ3 ሳምንት በፊት አሰላ ከተማ የገጠር ቀበሌ ቆኒቻ ደንካካ የሚባል አካባቢ በጠራራ ጸሃይ የአርሶ አደሮቹን ከብቶች ዘርፎ የሄደው ይሄ አካል ንብርቱን ለማዳን በሞክረው ነዋሪ ላይም ጥቃት መሰንዘራቸውን ሳይጠቁሙ አላለፉም።
አሁንም በአካባቢው ይሄው ቡድን በብዛት እንደሚገኝ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ ህብረተሰቡም ከዚህ ቡድን ጋር ከመፋጠጥ ውጪ የሚያደርገው ምንም ማድረግ አልቻለም ሲሉ ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 ገልጸዋል።