በሐዋሳ ከተማ ከንቲባ የግል ጠባቂ የታፈነችው ወይዘሪት ጸጋ በላቸው እስካሁን ያለችበት ሊታወቅ አለመቻሉን የኢትዮ 360 ምንጮች ገለጹ።
የዳሽን ባንክ የሂሳብ ሠራተኛ የሆነችው ወይዘሪት ጸጋ በላቸው በከንቲባው ጠባቂ የታገተችው ግንቦት 15/2015 ከሥራ ወደ ቤት እየተመለሰች ባለችበት ወቅት እንደነበር ያነሳሉ።
ታፋኟ የወልቂጤ ከተማ ተወላጅ ስትሆን ወደ ሀዋሳ ከተማ የመጣችውም ባለፈው ዓመት ዳሽን ባንክ ተቀጥራ ለሥራ እንደሆነም አስታውሰዋል።
የተጠላፊዋ ቤተሰቦች ጉዳዩን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በማሳወቅ ክትትል ላይ ቢሆኑም እስካሁን ግን የተጠላፊዋ ደብዛ ሊገኝ አልቻለም ባይ ናቸው።
ይህ አፈና ከተፈጸመ ሳምንት የሞላው ቢሆንም ጉዳዩ ወደ ህዝብ ጆሮ እንዳይደርስ ተደርጎ እንደቆየም ሳይጠቁሙ አላልፉም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በየአካባቢው በኦህዴዱ ሃይል የሚደረገው አፈና አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ሳይጠቁሙ አላለፉም።
በብዙ ስራዎቹ የሚታወቀው አርቲስት ተሾመ አየለ በዚህ ሃይል ትላንት ሲታፈን የፍኖተ ህይወት በጎ አድራጎት ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ንጉሴ ዋለልኝም በዚሁ ስብስብ ወደ አልታወቀ ስፍራ ታፍኖ መወሰዱን አመልክተዋል።
ታፍነው በየቦታው እየተጋዙ ያሉ ንጹሃን ዜጎችም በየማጎሬያው ያለምንም ምግብና ውሃ እንዲሰቃዩ እየተደረጉ መሆኑንም ነው ምንጮቹ ያመለከቱት።
ምናልባትም በአንድ ቦታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንዲታጎሩ ከመደረጉ ጋርም ተያይዞ ምናልባትም ንጹሃን ዜጎቹ ለተለያዩ በሽታዎች ሊጋለጡ ይችላሉ ሲሉም ምንጮቹ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።