በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤትና የግል መኖሪያ ቤቶች ግብር ባልከፈሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ቅጣት መተላለፉን የኢትዮ 360 ምንጮች አስታወቁ።
አዲሱ የቅጣት ውሳኔ ከግንቦት አንድ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን መቀመጡንም ያነሳሉ።
እስካሁን ግብሩን ላልከፈለ የከተማዋ ነዋሪ ከግንቦት 1 ጀምሮ 5 በመቶ ቅጣት ሲጣልበት ይሄ ቅጣት ከሰኔ 1ጀምሮ ደግሞ ወደ 10 በመቶ ከፍ እንዲልም ውሳኔው ላይ መቀመጡን ተናግረዋል።
ከሀምሌ 1 ጀምሮ ደግሞ ይሄው ቅጣት የክፍያውን እጥፍ ባስቀመጠ መልኩ ወደ 100 በመቶ የሚያድግ መሆኑን ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ ይሄ ቅጣትን በተወሰነ ደረጃ ለማስቀረት ቀኑን ሙሉ ቀበሌና ወረዳዎችን አጨናንቆና ስራውን ፈቶ ቢውልም ትርፍ የሆነው የቀበሌ ካድሬ መቀለጃ መሆን ነው ይላሉ።
ህብረተሰቡ በዛ ደረጃ ሲንገላታ በየቀበሌው ያለው ካድሬ ግን በቀን እያስተናገደ ያለው 10 ያህል ሰዎችን ብቻ መሆኑን ያነሳሉ።
ከዛም አልፎ ተራው ደርሶት የተሟላ መረጃውን ያቀረበ ነዋሪ ለመሃንዲስ አንድ ሺ ብር እንዲከፍ ግዴታ መቀመጡን አመልክተዋል።
ነገር ግን አንድ ሺ ብሩን በግፍ የተነጠቀው ነዋሪ የተባለውን ገንዘብ ቢከፍልም መሃንዲስ የሚባለው አካል ግን አይላክለትም ሲሉ የሚሰራውን ወንጀል ያሳያሉ።
እያንዳንዱ ነዋሪ የሚከፍለው ገንዘብ የሚወሰንለት ይዞት በቀረበው ዶክመንት መጠን መሆኑንም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
ይሄንን ክፍያ ያልፈጸመ የከተማዋ ነዋሪ ከመስከረም በኋላ መኖሪያ ቤቱን እንደሚነጠቅ እያወቀ ከክፍያው በላይ በመንገላታት እየከፈለው ያለው መስዋእትነት በዝቷል ብለዋል።
ምናልባትም ህዝቡ በጋራ ቆሞ አንከፍልም ወደሚል አቅጣጫ ካልሄደና ይሄንን ህገወጥ አካሄድ መከላከል ካልቻለ መቀር መቺው ጊዜ ቤት አልባ መሆን ብቻ ሳይሆን ከዚህም የከፋ አደጋ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል