በአፋር ክልል በሾላ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ታጉረው የሚገኙትና ቁጥራቸው ከ800 በላይ የሚሆን የአማራ ተወላጅ የመከላከያ አባል የነበሩና የፋኖ ህዝባዊ አባላት ሕይወታቸው በከባድ አደጋ ላይ መውደቁን ለኢት 360 ገለጹ።
በወታደራዊ ካምፑ ከታገቱ አንድ አመት እንደሆናቸው የሚናገሩት አባላቱ በካምፑ ውስጥ ምግብ፣ውሃና አልባሳትን ተከልክለው በመከራ ውስጥ መሆናቸውን ይናገራሉ።
በቀን አንዳንድ ኮቾሮ እየተሰጣቸው አንድ ቦታ የታጎሩት የአማራ ተወላጆች ለእለት ማረፊያ በማጣታቸው በቅጠልና በእንጨት ለመስራት መገደዳቸውን ይናገራሉ።
ከሁሉም እየከፋ የመጣው ደግሞ በየጊዜው የሚታመሙ ሰዎች መብዛትና ምንም አይነት የህክምና አገልግሎት አለመኖሩ ነው ይላሉ።
በተለይ ደግሞ በአካባቢው ያለው ሙቀት የበለጠ መከራቸውን እንዳከፋባቸው ተናግረዋል።
የታጎሩበትን ካምፕ እየጠበቀ ላለው ሃይል ጥያቄ ለማቅረብ ቢሞክሩም ምልሽ ግን ማግኘት እንዳልቻሉ ነው ለኢትዮ 360 የገለጹት።