በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ውጪ ለመውጣት የሚሞክሩ ሰዎች አላግባብ የሆነ ገንዘብ እየተጠየቁ መሆኑን መንገደኞቹ ለኢትዮ 360 ገለጹ።
መንገደኞቹ ወደ ተለያዩ ሃገራት ያደርጓቸው የነበሩት ጉዞዎች አላግባብ ክፍያ በመጠየቃቸው ብቻ ጉዟቸው ለቀናት መጓተቱን ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ አስፍረዋል።
እያንዳንዱ መንገደኛ ለሚያደርገው ጉዞ ከኢሚግሬሽን ሰራተኞች በትንሹ ከ10ሺ እስከ 30ሺ ብር ገንዘብ እንደሚጠየቁም ተናግረዋል።
ይሄ ገንዘብ ሲጠየቅ ደግሞ መንገደኛው ተጨማሪ አገልግሎት እፈልጋለሁ ብሎ ሳይሆን መሄድ ከፈለክ ይሄን ያህል ገንዘብ መክፈል አለብህ የሚል ህገወጥና አይን ያወጣ የሌብነት ጥያቄ ከነዚሁ የስርአቱ ሰራተኞች ስለሚቀርበለት ነው ይላሉ።
ትኬት ወደ ቆረጡበት ሃገር እንዳይሄዱ የተከለከሉና ገንዘብ አምጡ የሚባሉት መንገደኞች የሚጠየቁት ብር እንዲቀነስላቸው የኢሚግሬሽኑን የሌቦች ስብስብ የሚያሸማግል ሰውም በመሃል መኖሩን ሳይጠቁሙ አላለፉም።
በአጠቃላይ አሁን ላይ በአየር መንገዱ ውስጥ ያለው አይን ያወጣ ሌብነትና ህገወጥ አሰራር የሃገር ውስጥ መንገደኛውን ብቻ ሳይሆን የውጭ ሃገር ዜጎችንም ጭምር ዋጋ እያስከፈለ ነው ሲሉ በአየር መንገዱ ላይ የተደቀነውን አደጋ አመልክተዋል።