የደቡብ ክልል በሚል አዲስ ተመሰረተ የተባለው ክልል የመንግስት ሰራተኛውን ከግምት ባስገባ መልኩ አለመደራጀቱ ዋጋ እያስከፈላቸው መሆኑን ሰራተኞቹ ለኢትዮ 360 ገለጹ።
ማህበሩ የቀድሞው የደቡብ ክልል በአራት ክልሎች መደራጀትን ተከትሎ በመንግስት ሰራተኛው ላይ እየደረሰ ያለው በደል ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት እያካሄደ ነው ሲሉም ምንጮቹ ተናግረዋል።
ነገር ግን ማህበሩም ሆነ ሰራተኛው መብቱን በተለያየ መንገድ እየጠየቀ ባለበት በዚህ ሰአት ግን የደቡብ ኢትዮጵያም ሆነ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በሚል የተመሰረቱት ክልሎች አመራሮች ግን የሰራተኛውን ጉዳይ ለአፍታም ማሰብ አይፈልጉም ሲሉ ያለውን እወነታ አስቀምጠዋል።
ይልቁንም የሰራተኛውን ችግር ከመፍታት ይልቅ ለሹመት መሽቀዳደም እና ስራ ጀምረናል በሚል ማህበራዊ ሚዲያውን ማጨናነቅን የዘወትር ስራቸው አድርገውታል ብለዋል ሰራተኞቹ በመረጃቸው።
የክልል አደረጃጀትን በበላይነት ለመምራት በህግ ስልጣን የተሰጠው ፕሮጀክት ጽህፈትቤት የሰራተኛውን ጉዳይ ጆሮ ዳባ ልበስ ያለ ይመስላል።
በፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተሰራ የተባለው የሰራተኞች የስራ ድልድልም ቢሆን ከመስፈርቱና ከህጉ ጋር የተጣረሰ ነው ሲሉ ሰራተኞቹ በመረጃቸው ተናግረዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰራተኞች ወደ ተቃውሞ መግባታቸውን አመልክተዋል።
ሰራተኞቹ ከተቃውሞም ሌላ በድልድል መስጫ መስፈርቱ ላይ ያቀረቡት ቅሬታ በሁለት ቀናት ምላሽ ያገኛል ቢባልም ቅሬታው ከቀረበ ግን ከ20 ቀን በላይ ሆኖታል ብለዋል።
የሰራተኛውን መብት ይዞ ከክልል እስከ ፌደራል የሰራተኛውን መብት ለማስከበር እየለፋ ያለው የሰራተኛ ማህበሩ ከሁሉም አካል ምላሽ የማያገኝ ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንደሚገደድም ነው ሰራተኞቹ ለኢትዮ 360 በላኩት መረጃ ላይ ያሰፈሩት።